የሰው ልጅ እንስሳት በህይወት ዘመኑ ከሚያጋጥሙት እክሎች መሀከል አንዱ የጤና መታወክ መሆኑን ሁላችንም በዕለት ተዕለት ኑሮአችን የምናውቀው እውነት ነው፡፡ የህክምና ሙያም የተለያዩ የጤና መታወኮች መፍትሔ የሚያገኙባቸውን ሂደቶች የሚያመቻችና በብዙ ሀላፊነት የሚሰራ፤ ጥልቅ እውቀትና ትጋት የሚጠይቅ የከበረ ሙያ ነው:: ይሁን እንጂ በብዙ ትጋትና እውቀት የሚሰሩ ባለሙያዎች እንዳሉ ሆነው አልፎ አልፎ ግን በቸልተኝነትና በብቃት ማነስ አልያም በሌላ ምክንያት የህክምና ስህተቶች ተፈጥረው ሰዎች ሲጎዱ ይስተዋላል፡፡ ሞትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳቶች ሁሉ የሚፈጠሩት በህክምና ስህተት ነዉ ማለት ግን እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል:: ምክንያቱም ነፍስ የፈጣሪ ናት: በከፍተኛ ጥንቃቄና ሙያዊ ብቃት ህክምና ተሰጥቶም ጉዳትም ሆነ ሞት ሊኖር ይችላልና::...
በዛሬው ርዕሰ ጉዳያችንም የህክምና ስህተት ከህግ መነፅር አንፃር ምን እንደሚመስል ለማየት እንሞክራለን፡፡
የህክምና ስህተት ማለት:ህክምና መሰጠት ሲገባው አለመሰጠት፤ የተሳሳተ መድሀኒት ለታካሚ መስጠት፤ በቀዶ ህክምና ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶች፤ ባእድ ነገሮችን በታካሚው አካል ውስጥ መተው: መወገድ ያለበትን አካል ትቶ ጤናማዉን ማስወገድ: የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ ይህም ስህተት ከሀገራችን ህጎች አንፃር በሁለት ክፍል እናያለን፡፡
ክፍል 1
የህክምና ስህተት ከፍትሃብሔር ሕጋችን አንፃር
ከአንቀጽ 2639-2652 ሥለ ሕክምና ወይም ሆስፒታል ውል(contract of hospitalization) ተደንግጓል!
በታካሚውና በሕክምና ባለሙያው ወይም ከሕክምና ተቋሙ ጋር የሚኖረው የሕክምና ግንኙነት ውል ነው!
የውል ግንኙነት በማይኖርበት ጊዜ ግንኙነታቸው ከውል ውጭ ኃላፊነት ሕግ መሠረት ይታያል! (አንቀፅ 2037)
በመሆኑም በውሉ መሰረት ታካሚው ለሚሰጠው አገልግሎት ተገቢውን ክፍያ የመፈፀም ግዴታ አለበት!
ባለሙያው/ተቋሙ ለታካሚው የአገልግሎት ደረጃውን የጠበቀ ወይም የሕክምና ደንቦችን ያከበረ ወይም መሠረት ያደረገ የሕክምና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት!
ይህ ሳይሆን ግን የህክምና ስህተት ከተፈጠረ የሕክምና ተቋሙ ወይም ባለሙያው በታካሚው ላይ ላደረሰበት ጉዳት ተገቢውን ካሣ ለመክፈል ከውል የመነጨ ፍትሃብሔራዊ ተጠያቂነት ይኖርበታል!
እንዲሁም በአንቀጽ 2126፣2127፣2129ና 2130 መሰረት የሕክምና ግንኙነቱ በውል በማይመሠረትበት ወቅት ለምሳሌ ለድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ወይም በድሃ ደንብ ነፃ ህክምና በሚሰጥበት ሁኔታ ተቋሙ ወይም ባለሙያው በታካሚው ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ከውል ውጭ ኃላፊ በመሆን ባለሙያዎቹ ላደረሱት ጉዳት ኃላፊነት የገንዘብ ካሳ የመክፈል (vicarious liability) ወይንም ፍትሐቤራዊ ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል፡፡
በክፍል 2 ም ስለህክምና ስህተትና የወንጀል ተጠያቂነት ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡
"… ህክምና የከበረውን የሰውንና የእንስሳትን ህይወት ከአደጋ ለመታደግ የቆመ የከበረ ሙያ ነው!!
በመሆኑም የሙያውን ህግና ደንብ ተከትሎ መስራትም ለሙያው ከፍተኛ ክብር መስጠት ነው!!"
"ህግን የሚያዉቅ ትውልድ መብቱንና ግዴታውን ያውቃል:
ለሀገር ግንባታ መልካም አስተዋፅኦ ይኖረዋል!!"
ለሕግ፤ ለፍትሕና ለርትዕ እንሰራለን!!





